ፍላሽ ወይም ሚሞሪ ካርድ ፎርማት ስናደርግ የምንመርጣቸው FAT32, NTFS እና exFAT ምንድን ናቸው? ልዩነታቸውስ?

ፍላሽ ወይም ሚሞሪ ካርድ ፎርማት ስናደርግ የምንመርጣቸው FAT32, NTFS እና exFAT ምንድን ናቸው? ልዩነታቸውስ?
FAT32፣ NTFS እና exFAT ሁሉም የፋይል ሲስተሞች ሲሆኑ እንደ ሃርድ ድራይቭ፣ ፍላሽና SD ካርዶች ላይ መረጃን ለማደራጀት፣ ለማከማቸትና ለመደርደር ያገለግላሉ።
አንድ በአንድ እንያቸው....
- FAT32 (File allocation Table 32)
FAT (file allocation system) ረጅም እድሜ ያለው ቢሆንም (FAT12, FAT16) እስከዛሬ ድረስ የምንጠቀምበት የ FAT አይነት FAT32 ነው። FAT32 የተዋወቀውም 1996 እ.ኤ.አ. በማይክሮሶፍት Windows 95 ላይ ነበር።
(FAT ከ1996 ቀደም ብሎ ነው የተሰራው።)
የካሜራዎችና የጌም ኮንሱሎች ጨምሮ በሁሉም የእስቶሬጅ መሳሪያዎችና ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ላይ compatible ስለሆነ እስከዛሬ ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል። ነገር ግን የሚይዘው ትልቁ የፋይል መጠን 4GB ብቻ ስለሆነና ከ2TB በላይ size የሚይዙ ዲቫይሶች ላይ ስለማይሰራ ሌሎች የፋይል ሲስተም አይነቶች መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ችሏል።
ለምሳሌ 8GB ፍላሽ በFAT32 ፎርማት ብናደርገው ከ4GB በላይ size ያለው ፋይል ማስቀመጥ አንችልም። ስለዚህ ከ4GB በላይ የሆነ ፋይል ሲያጋጥመን በሌሎች ፋይል ሲስተሞች format ማድረግ ይኖርብናል።
- NTFS (New Technology File System)
NTFS በ1993 አ.ም Windows NT ሲተዋወቅ አብሮ የተዋወቀ ሲሆን ከFAT የተሻለና ዘመናዊ የፋይል ሲስተም አይነት ነው።
እስከ 16 exabyte መጠን ያለው ፋይል የመያዝ አቅም ሲኖረው እስከ 256 TB size የሚይዙ ዲቫይሶች ፎርማት ማድረግ እንችላለን።
NTFS ከWindows 2000 ጀምሮ ባሉት የዊንዶስ ቨርዥኖች የተለመደ የፋይል ሲስተም ሲሆን system crash ወይም የpower failure በሚያጋጥምበት ጊዜ ፋይል በቀላሉ recover ለማድረግ ያስችላል። ይህም ተመራጭ ያደርገዋል።
ከዊንዶውስ ውጭ ባሉ ሌሎች ፕላትፎርሞች ላይ ግን ብዙም ያልተለመደ ስለሆነ ከኢንቫይሮመንት ኢንቫይሮመንት ያለውን መስተጋብር ውስን እንዲሆን ያደርገዋል።
- exFAT (Extended File Allocation Table)
ይህም በማይክሮሶፍት ኩባንያ በ2006 የተሰራ ሲሆን በFAT32 ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመድፈን ነው ዲዛይን የተደረገው።
ከሌሎች በብዙ እጥፍ የበለጠ ፋይል የመያዝና ዲቫይሶች ላይ የሚሰራ ሲሆን 16 exabyte መጠን ያለው ፋይል የመያዝ አቅም አለው። እንዲሁም እስከ 128 petabyte size የሚይዙ ዲቫይሶች ላይ በትክክል ይሰራል።
ከዊንዶውስ በተጨማሪ በሌሎች ፕላትፎርሞች እንደ macos እና Linux ላይ የሚሰራ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያላቸው ፍላሾችን፣ ሚሞሪ ካርዶችን እንዲሁም ሃርድ ዲስኮችን ፎርማት ለማድረግ ይጠቅመናል።
በአጠቃላይ እነዚህን የፋይል ሲስተሞች የምንመርጠው ልንጠቀምባቸው እንደምንችለው የመሳሪያ አይነቶችና የኦፕሬቲንግ ሲስተም አይነቶች ነው።
NTFS የላቁ ባህሪያት ላሉት የዊንዶውስ ስርዓቶች ተስማሚ ሲሆን ፋይላችን corrupt ቢሆን ወይም crash ቢያደርግ recover ለማድረግ ይመረጣል። exFAT ደግሞ የተለያዩ ፕላትፎርሞች ላይ እንዲሰራ እንዲሁም ትላልቅ ፋይሎችን በተንቀሳቃሽ የእስቶሬጅ መሳሪያዎች ላይ ለማስቀመጥ ጥሩ ምርጫ ነው።
FAT32 አሁንም በተወሰኑ ሁኔታዎች ጥቅም ላይ ይውላል። ነገር ግን በፋይል እና የድምጽ መጠን, ደህንነትና የፋይል መልሶ ማግኛ ሁኔታዎች ላይ ግን ከሌሎቹ ያነሰ አቅም አለው።
What's Your Reaction?






